Wednesday, March 22, 2017

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፡ በእንጦጦ ተራራ ላይ ግዙፍ ሆስፒታል ልትገነባ ነው

·         ሆስፒታሉ፣ የሜዲካል እና የነርሲንግ ዩኒቨርስቲን ያካትታል፣
·         ታሪክን ያንጸባርቃል፤ ሥነ ምኅዳርን የሚጠብቅ ቴክኖሎጂ ይጠቀማል፣
·         ለሀገሪቱ የሕክምና ቱሪዝም ፍሰት አስተዋፅኦ ያደርጋል፣
 ሰንደቅ፤ መጋቢት 13 ቀን 2009 .
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ ተዋሕዶ ዲፕሎማቲክ ሜዲካል ሲቲ የተሰኘ ኹለገብ የሕክምና ማዕከል 400 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚገነባ ያስታወቀ ሲኾን፤ የፕሮጀክት ስምምነቱንም፣ ጀንደሪ ሜጋኮርፕ ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋራ መፈራረሙን ገለጸ። 


ስለ ፕሮጀክቱ ስያሜና ሒደት ማብራሪያ የሰጡት የኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ የመግባቢያ ሰነዱን ከድርጅቱ ጋራ ለመፈራረም፣ የተለያዩ የጥናት ሥራዎች መሠራታቸውንና የቦታ መረጣም መካሔዱን ጠቅሰው፤ የፕሮጀክቱ ስያሜም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ባሕርይ በአገናዘበ መልኩ የተሰጠ መኾኑን፣ ስምምነቱ በኮሚሽኑ አዳራሽ በተፈረመበት ወቅት ገልጸዋል። 
በይዘቱ፣ በጠቀሜታውና በፋይናንስ ረገድ ግዙፍና በደረጃውም የዓለም የጤና ድርጅትን መስፈርት በማሟላት ተግባራዊ እንደሚኾን የጠቆሙት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር / አግደው ረዴ፥ በዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊ ከሚኾነው ድርጅት ጋራ፣ በመጪው ሚያዝያ ወር የግንባታ ውል ከተፈጸመ በኋላ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጸሎትና ቡራኬ የመሠረት ድንጋዩ እንደሚቀመጥ አስታውቀዋል። 

ኹለገብ የሕክምና ማዕከሉ፥ በአዲስ አበባ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ፣ በእንጦጦ ተራራ ላይ በሚገኝ 210ሺሕ ካሬ ሜትር አጠቃላይ ስፋት ባለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ቦታ ላይ ነው፣ የሚያርፈው። ከእዚኽም ውስጥ፣ 67ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ በአንድ ጊዜ 600 ሕሙማንን አስተኝቶ ማከም የሚያስችል ዘመናዊ ሆስፒታል፤ 28ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ፣ የሜዲካል እና የነርሲንግ ዩኒቨርሲቲ ሕንጻዎች እንደሚገነቡ፣ ኮሚሽነር / አግደው አስረድተዋል፤ ድጋፍ ሰጭ ኾነው የሚያገለግሉ የአስተዳደር ሕንጻዎች፣ የውስጥ ለውስጥ መሠረተ ልማቶች፣ የመንገድ፣ የሜካኒካል፣ የአይሲቲ ሥራዎችን እንደሚያጠቃልልም ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል።  

የሌጀንደሪ ሜጋኮርፕ ድርጅት ተወካዮች በበኩላቸው፣ ሀገሪቱን ከምትወክለው ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ጋራ በትብብር ለመሥራት እዚህ ደረጃ በመድረሳችን ትልቅ ኩራትና ክብር ይሰማናል፤ ብለዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሃይማኖታዊ ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት እንደሚያካትትና የአካባቢውን የዕፀዋትና ደን ሥነ ምኅዳር የሚጠብቅ ትልቅ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም መኾኑን አስረድተዋል። 

በግንባታው ወቅት በጊዜአዊነት 10ሺሕ800 ለሚኾኑ ሰዎች አዲስ የሥራ ዕድል ሲከፍት፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ደግሞ፣ 5ሺሕ ያህል ባለሞያዎች፣ በቋሚነትና በኮንትራት ተጨማሪ የሥራ መስክ በማስገኘትና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍ የራሱ የኾነ ሚና ይኖረዋል፤ በትምህርቱም ዘርፍ፣ በየዓመቱ ለመቶ ያህል የሜዲካልና 200 በላይ ለሚኾኑ የነርሲንግ ተማሪዎች የትምህርት ዕድል በመክፈት ለማኅበረሰቡ የላቀ አገልግሎትና የተሻለ ሕክምና የሚሰጥ የተማረ የሰው ኃይል እንደሚያፈራ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፤ አያይዘውም፣ ሀገሪቱ፣ የሕክምናውን ሞያ ከሥነ ምግባሩ ጋራ የተካኑ ዶክተሮችን እንድታፈራ በማስቻል፣ ለሕክምና ቱሪዝም ፍሰት አስተዋፅኦ ያደርጋል፤ ብለዋል ኮሚሽነሩ። 

በመሪ ዕቅዱ መሠረት፥ አምስት የግንባታ ምዕራፎች ያሉት ፕሮጀክቱ፣ የቁፋሮ ሥራው በቀጣዩ ዓመት ኅዳር 2010 እንደሚጀመርና በአምስት ዓመታት ለማጠናቀቅ መታቀዱ የተመለከተ ሲኾን፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም፣ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አማካይነት የላቀና ዘመኑን የሚዋጅ ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችላት ተገልጿል። 

No comments:

Post a Comment